የሆሄ የሥነ ጽሑፍ ሽልማት የመጨረሻ ዕጩ ምርጥ መጸሕፍት ታወቁ፡፡
ኖርዝ ኢስት ኤቨንትስ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተ መጻህፍት ኤጄንሲ ጋር በመተባበር እየተዘጋጀ የሚገኘው
የሆሄ የሥነ ጽሑፍ ሽልማት የ2008 ዓ.ም ምርጥ መጻህፍት ዕጩዎች ይፋ ሆነዋል፡፡ የሽልማት ዝግጅቱ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ
ከተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተውጣጡ የሥነ ጽሑፍ ምሁራን ፣ ታዋቂ ደራሲያን እንዲሁም የሥነ ጽሑፍ ባለሙያዎች
የተውጣጣ የዳኞች ኮሜቴ በማዋቀር ለውድድሩ የተመዘገቡ መጻሕፍትን ሲገመግም ለ 5 ወራት ቆይታ አድርጓል፡፡
በዚህ ዓመት የሆሄ ሽልማት በ2008 ዓ.ም የታተሙ በረጅም ልብወለድ ዘርፍ 23 መጻሕፍት ፣ በልጆች መጻሕፍት ዘርፍ 12 እንዲሁም
በግጥም መጽሀፍት ዘርፍ 39 መጽሐፍት ለውድድር ተመዝግበው ከእያንዳንዱ ምድብ 5 ምርጥ መጻሕፍትን ለመለየት በዳኞች ጥልቅ
ግምገማ ሲካሄድ ቆይቷል፡፡በዚህም መሰረት በረጅም ልብወለድ ዘርፍ የሚከተሉት መጻሕፍት ምርጥ 5 መጻህፍት ተብለው
ተመርጠዋል፡፡
– ዝጎራ (ዶ/ር አለማየሁ ዋሴ)
-የስንብት ቀለማት (አዳም ረታ)
– መጽሐፉ (ሰብለወንጌል ፀጋ)
– ውስብሳቤ (ያለው አክሊሉ)
– የሱፍ አበባ (ሀብታሙ አለባቸው)
በግጥም መጻሕፍት ዘርፍ የሚከተሉት አምስት መጻሕፍት በዕጩነት የተመረጡ ናቸው፡፡
– ኑ ግድግዳ እናፍርስ (ኤፍሬም ስዩም)
– የጎደሉ ገጾች (ትዕግስት ማሞ)
– የተስፋ ክትባት (ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ)
– ፍርድ እና እርድ (አበረ አያሌው)
– እንቅልፍ እና ሴት (በላይ በቀለ ወያ)
በልጆች መጻሕፍት ዘርፍ የምድቡ ዳኞች 3 መጻሕፍትን የመረጡ ሲሆን መጻሕፍቱም የሚከተሉት ናቸው፡፡
– የቤዛ ቡችላ (አስረስ በቀለ)
– የአይጦችና የድመቶች ሰርግ (ታለጌታ ይመር)
– ዋናተኛዋ ሶሊያና (አስረስ በቀለ)
ከየዘርፉ አንደኛ የሚወጡትን የመጨረሻዎቹን አሸናፊዎች ለመለየት በዳኞች ከሚደረገው ዳግም ግምገማ በተጨማሪ ከአንባቢያን
የሚሰበሰበው ድምጽ ከአጠቃላይ ውጤቱ 20 % የሚይዝ ሲሆን አንባቢያን በስልክ ቁጥር 09 88 12 12 12 በአጭር መልዕክት
አንደኛ መውጣት ይገባዋል የሚሉትን መጽሐፍ ርእስ ከሀምሌ 20 እስከ ነሐሴ 20 2009 ዓ.ም ድረስ በመላክ መሳተፍ ይችላሉ፡፡
በተጨማሪም በሽልማቱ የፌስቡክ ገጽ www.facebook.com/Hohe-Awards እንዲሁም በሽልማቱ የትዊተር አድራሻ
@HoheAwards መጽሐፍቱን ለመምረጥ በተዘጋጀው ገጽ አማካኝነት ምርጫቸውን ማሳወቅ የሚችሉበት እድል ተመቻችቷል፡፡
የሽልማት ፕሮግራሙ ከመጻሕፍቱ በተጨማሪ ለሥነ ጽሑፍ እድገት እና ለንባብ ባህል መዳበር የላቀ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ግለሰቦች እና
ተቋማት በዝግጅቱ ላይ እውቅና የሚሰጣቸው ሲሆን የሽልማት ዝግጅቱም ነሐሴ 22 2009ዓ.ም ከምሽቱ 12፡00 – 2፡00
በብሔራዊ ቴያትር አዳራሽ ይካሄዳል፡፡ የሽልማት ዝግጅቱ በቴሌቭዥን በኢትዮጵያ እና በመላው አለም ላሉ ተመልካቾች የሚተላለፍ
ይሆናል፡፡
ለተጨማሪ መረጃ የዝግጅቱን አስተባባሪዎች ማግኜት ይቻላል፡፡ ዘላለም ምህረቱ 09 19 39 79 77 ኤፍሬም ብርሀኑ 09 88 12 12
12 ፡፡
የሆሄ የስነ ጽሑፍ ሽልማት እስካሁን ድረስ በእናንተ በኩል የሽልማት ፕሮግራሙን በማስተዋወቅና መረጃዎቹን ለህዝብ በማድረስ ለተደረገልን
ትብብር ከልብ የመነጨ ምስጋና እና አክብሮታችንን ለመግለጽ እንወዳለን፡፡ ይህንንም መግለጫ የሚዲያ ሽፋን እንዲሰጥልን እየጠየቅን
የዝግጅቱን ተከታታይ ሂደቶችንም በየጊዜው እንደምናሳውቃችሁ ለማስታወስ እንወዳለን፡፡